
በጀብዱዎች የተሞላው ሄልዲቨርስ 2 ከተጀመረበት ጊዜ አንሥቶ የብዙ ተጫዋቾችን ቀልብ መግዛት የቻለ ቪዲዮ ጌም መሆኑ የታወቀ ነው ፥ ሆኖም ግን የመጀመርያው ምዕራፍ ላይ ተጫዋቾች ኦፍላይን መጫወት የሚችሉበት አማራጭ አለመኖሩ እና ጌሙን ለመጫወት ሁሌም የኢንተርኔት ግንኙነት (PSN) ማስፈለጉ ቅሬታዎችን አስነስቶ ነበር። በዚህም የተነሳ ሶኒ የተጫዋቾችን ቅሬታ ግምት ውስጥ በማስገባት መፍትሄን አበጅቷል።.
ዛሬ ፣ ስለ ሄል-ዳይቨርስ 2 እና ስለ አዲስ ስለተለቀቀው አስደናቂ ሞድ የተሰማው አስገራሚ ዜና በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሰፊው እየተንሸራሸረ እና አነጋጋሪነቱ እየጨመረ ይገኛል። እስኪ አስቡት የስታር ዋርስ ገፀ-ባህርያት በሄል-ዳይቨርስ 2 የውግያ አውድማዎች ላይ ለኢንተርጋላክቲክ ዲሞክራሲ ሲፋለሙ!? ስታር ዋርስ እና ሄል-ዳይቨርስ አንድ ላይ? አዎ ፣ ምኞት አይደለም መሬት ላይ የወረደ አስደሳች ዜና ነው ፥ ስታር ዋርስ ሞድ ለሄል-ዳይቨርስ 2 ተዘጋጅቷል። ይህ በቶስትድ ሹዝ (Toasted Shoes) ዩ-ቲዩብ ቻናል ላይ ይፋ የተደረገው ሞድ ፣ ገፀ-ባህሪያትን ወደ ወታደርነት መቀየር ብቻ ሳይሆን ፣ ጠላቶችን እና መርከቦችን መቀየር ሁሉ የሚያስችል ነው። ይህ ዜና ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ ብዙ የቪዲዮ ጌሙ አድናቂዎች እና ተጫዋቾች ይህን ሞድ ሄል-ዳይቨርስ 2 ላይ እንዴት መጫን እንደሚችሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
ይህ ሞድ ለስታር ዋርስ እና ሄል-ዳይቨርስ 2 አድናቂዎች የሁለቱን አፅናፈ-ዓለማት ውህደት የሚያስቃኝ ሲሆን ፥ ቀድመው ሄል-ዳይቨርስ 2 ውስጥ ይገኙ የነበሩ መርከቦች ፣ የስታር ዋርስ የጠፈር መንኮራኩሮችን መልክ የሚይዙ ሲሆን አስደናቂው ጦርነትም ከባለ አራት እግር ሮቦት ታንኮች (AT-ATs) እና ብረት ለበስ ወታደሮች (droids) ጋር ይሆናል። በአጭሩ የስታር ዋርስን የጦር ግንባር በሄል-ዳይቨርስን 2 ማጣጣም መቻል ማለት ነው።
ሞዱን እንዴት ማግኘት ይቻላል?
የስታር ዋርስ ሞድ እስካሁን በይፋ ያልተለቀቀ ሲሆን ይህም ፣ ተጨዋቾች ያለምንም እክል መጫወት ይችሉ ዘንድ አንዳንድ ማስተካከያዎች እየተደረጉበት በመሆኑ ነው። የሞዱ ፈጣሪ የሆነው ቶስትድ ሹዝ በቅርቡ እንደሚለቀቅ የተናገረ ሲሆን ፥ ለጊዜው ግን ተጨዋቾች ኔክሰስ ሞድስ (Nexus Mods) ላይ በመግባት ሌሎች ሞዶችን ማግኘት ይችላሉ።
ሄልዲቨርስ 2 ላይ ሞዶችን ለመጫን የሚከተሉትን ሂደቶች ይከተሉ፦
ወደ ኔክሰስ ሞድስ (Nexus Mods) ድረ-ገፅ በማምራት ፣ ፋይሉን ያውርዱ
በመቀጠል ፣ በሞዱ ድረ-ገጽ ላይ የተቀመጠውን የአጫጫን መመሪያ በመከተል ይጫኑ
በመጨረሻም ፣ የጌሙ ማስተካከያ አማራጮች ውስጥ በመግባት ሞዱ መጀመሩን ያረጋግጡ።
ይህ የስታር ዋርስ ሞድ ልዩ ምስሎችን እና ገፀ-ባህሪያትን የሚጨምር እንጂ የጨዋታውን አካሄድ ወይም አጨዋወት የሚለውጥ አይደለም። በተጨማሪም እንደ ሃሎ እና ኪል-ዞን (Halo & Killzone) ያሉ ሌሎች ሞዶችም በቀጣይ ሊዘጋጁ እንደሚችሉ ይጠበቃል።