
ፎርትናይት ምዕራፍ 5 ክፍል 2 ፣ የማይረሳ ታሪክን አስቀምጦ የተገባደደ ሲሆን ፣ የግሪክ አፈታሪክ ጭብጦችን እና አቫተር ፡ ዘ ላስት ኤር ቤንደርን (Avatar, the Last Airbender) በማካተት ፣ የብዙ ሺ ተጨዋቾችን ልብ መግዛት የቻለ ምዕራፍም ነበር።
የክፍል 2 መገባደጃ ላይ እንደመድረሳችን ፣ ቀጣዩ ክፍል 3 ከፍተኛ ጉጉትን ፈጥሯል። እንደ ድህረ-ምጽዓት ዓለም ጭብጥ እና አዲስ አስገራሚ ሽርክናዎች በአዲሱ ክፍል ሊካተቱ እንደሚችሉ በቅርብ የተለቀቁ ፍንጮች ያመለክታሉ።
ስለዚህ ተጫዋቾች በአዲሱ ምዕራፍ ምን ይጠብቁ፦
የድህረ-ምጽዓት ዓለም ይዘት፡- ምዕራፍ 3 አውሎ ንፋስ እና የማይጨበጡ የአየር ሁኔታ ክስተቶችን የሚያስተናግድ ቅልጥ ያለ የበረሃ መልክዓ ምድርን እና አዳዲስ ገፀ-ባህሪዎችን ፣ ተልዕኮዎችን እና ሽልማቶችን ሊያስገኙ የሚችሉ ከሜታሊካ እና ፓይሬትስ ኦፍ ዘ ካሪቢያን ጋር የተደረጉ ሽርክናዎችን የሚያካተት ይሆናል።
የተጫዋቾች በይነገጽ፡- በአዲሱ ምዕራፍ የተሻሻለው በይነገጽ በጌሙ ውስጥ ነገሮችን የመግዛት ሂደትን ይበልጥ ቀላል ያደርጋል።
አዳዲስ ተሽከርካሪዎች፡- የጦርነት መኪናዎች እና የእንፋሎት ባቡር ያሉ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች የሚጨመሩ ይሆናል።
ገፀ-ባህሪያት፡- ማርቭል ጋላክተስ (Marvel's Galactus) እና ሎኪ የሚባሉት ገፀ-ባህሪያን ሊመለሱ ይችላሉ ተብሎ ይገመታል።
ፎርትናይት ይዞ እየመጣ ባለው አዲስ ምዕራፍ ፣ የተጫዋቾች የጨዋታ ተሞክሮ አስደሳች ሊያደርጉ የሚችሉ ጉልህ ለውጦች እና ማሻሻያዎችን ይዞ እየመጣ እንደሆነ የሚያጠራርር ጉዳይ አይደለም።
ፎርትናይት በኢፒክ ጌምስ የተሰራ የኦንላይን ጌም ሲሆን ፣ ተጫዋቾች የተለያዩ የጨዋታ አማራጮችን ፣ በተመሳሳይ የአጨዋወት ሂደት እና አተገባበር የሚያስተናገድ ቪዲዮ ጌም ሲሆን ፣ ሁለቱ የጨዋታ አማራጮችም፦
ሴቭ ዘ ዎርልድ (Save the World)፡- ተጫዋቾች ይዞታዎቻቸውን ለመጠበቅ ፣ ለአራት በመሆን ከጭራቆች (Zombies) ጋር የሚዋጉበት የቡድን ጨዋታ ሲሆን ፣ ይህም የጨዋታ አማራጭ እ.ኤ.አ 2017 ሐምሌ ወር ላይ ነበር የተለቀቀው። ይህም ሞድ ማይክሮሶፍት ዊንዶውስ ፣ ማክሮስ ፣ ፕለይስቴሽን 4 ፣ ፕለይስቴሽን 5 ፣ ኤክስቦክስ 1 እና ኤክስቦክስ X እና S የጨዋታ መድረኮች ላይ ይገኛል።
ባትል ሮያል (Battle Royale)፡- በዚህ አማራጭ እስከ 100 የሚጠጉ ተጫዋቾች አንድ ሰው እስከሚቀር ድረስ የሚዋጉበት የጨዋታ አማራጭ ሲሆን ፣ ይህም እ.ኤ.አ 2017 መስከረም ወር ላይ ነበር የተለቀቀው። ይህም ሞድ ከላይ የተጠቀሱት ሁሉም የጨዋታ መድረኮች ላይ እና ኒንቴንዶ ስዊች ፣ አይ.ኦ.ኤስ እና አንድሮይድ ላይ ይገኛል።