
ፎርትናይት በዚህ ክረምት አዳዲስ አስደሳች ይዘቶችን ይዞ እያመጣ ነው! በቅርቡ ከፓይሬትስ ኦፍ ዘ ካሪቢያን ጋር አስደሳች ሽርክናን መፍጠሩ የሚታወቅ ሲሆን ፣ ኢፒክ ጌምስ በዚህ አላበቃም ፣ ብዙ አስገራሚ ነገሮችን ይዞ በመምጣት ላይ ይገኛል። ሐምሌ 23 ባደረገው ዝማኔ ቴስላ ሳይበርትራክን እና ፎል ጋይስ የተባለ አነስተኛ ጌምን ያካተተ ሲሆን ፣ ከሁሉም በላይ የሚያስደንቀው ጉዳይ ግን ፣ ሁለት የጨመራቸው የዴድ ፑል እና የዎልቨሪን ገፀ-ባህሪዎች ናቸው።
አዲሱ ዴድ ፑል እና የዎልቨሪን ፊልም መለቀቅን ተከትሎ ፣ በርካታ ሽርክናዎችን ማድረጉን የቀጠለ ሲሆን ፣ ኤክስ-ቦክስ እነዚህ ሁለት ገጸ-ባህሪያትን መሰረት ያደረገ ሁለት መቆጣጠሪያዎችን አስተዋውቋል። ኢፒክ ጌምስ እነዚህን ሁለት ተወዳጅ ጀግኖች ፎርትናይት ላይ ማካተታቸው አስደሳች ዜና ሲሆን እንዴት እነዚህን ሁለት ገፀ-ባህሪዎች ማግኘት እንደሚቻል ቀጥለን እናያለን።
ዴድ-ፑል እና ዎልቨሪን ሊኖርዎ የሚገቡ ገፀ-ባህሪዎች ሲሆኑ ፣ ላልተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚገኙ በመሆናቸውም ፣ በፍጥነት የግልዎ ሊያደርጓቸው ይገባል።
ገፀ-ባህሪዎቹን እንዴት ማግኘት ይቻላል?
እነዚህን ገፀ-ባህሪዎች ፣ ጌሙ ውስጥ የሚገኘው መደብር ላይ ማግኘት የሚቻል ቢሆንም ፣ ተልዕኮዎች ወይም ውድድሮች ላይ በመሳተፍም በነፃ ሊገኙ ይችላሉ። እንዲሁም የውጊያ ማለፊያዎች ወይም የፕሮግራም ማለፊያዎች ላይ አልፎ አልፎ ሊገኙ ይችላሉ።
ኤፒክ ጌምስ የዴድ-ፑል እና ዎልቨሪን ገፀ-ባህሪዎችን ፣ እንዴት ማግኘት እንደሚቻል እስካሁን በይፋ የገለፁት ነገር ባይኖርም ፥ መረጃ አቀባዮች እንዳሉት ከሆነ ግን ፣ ገፀ-ባህሪዎቹ ሐምሌ 23 ፣ 2024 ከሚደረገው የጥገና ዝማኔ 30.30 በኋላ ፣ በፎርትናይት መደብር ውስጥ ሊገኙ እንደሚችሉ ጠቁመዋል። ምንም እንኳን ትክክለኛ ዋጋቸው ያልተረጋገጠ ቢሆንም ፣ ከ1500 እስከ 2000 ቪ-በክስ ባለው ክልል ውስጥ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል።.
እንደ ሃይፕ-ኤክስ ያሉ መረጃ አቀባዮች በለቀቋቸው ምስሎች መሰረት ፣ ሁለቱ ገፀ-ባህሪዎች ከተጨማሪ ማጌጫ ጥቅሎች ጋር እንደሚመጡም ጠቁመዋል፡-
- ኢሞት (ልዩ እንቅስቃሴ)
- የመቆፈሪያ ማስጌጫ
- የጦር መሳሪያዎች ማስጌጫ
- መሳሪያን ለማስጌጥ የሚሆን ተለጣፊ
የዎልቨርን እና የዴድ-ፑል ጭብጥ ያለው ግላይደር እና ፣ ለፌስቲቫል አድናቂዎችም የጊታር ማጌጫ ሊኖሩ እንደሚችሉ ፣ የወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል