
EA FC 25 ላይ አሸናፊ ለመሆን ፣ ኮከብ እና ታዋቂ ተጫዋቾችን ማሰለፍ ብቻ ላይ የሚወሰን ጉዳይ ሳይሆን ፣ ለሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የሚመጥኑ እና የተጠኑ የአሰላለፍ ስልቶችን መጠቀም እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ጥሩ የአሰላለፍ ስልትን መጠቀም የቡድንዎን አፈፃፀም ከፍ የሚያደርግ እና የተቃራኒ ቡድንን አፈፃፀም ማዳከም የሚያስችል ስልታዊ አካሄድ ነው። ከዚህ ቀጥሎ EA FC 25 ላይ ሊጠቀሟቸው የሚገቡ ሦስት ምርጥ አሰላለፎችን አዘጋጅተናል፦
4-2-3-1፡- ይህ አሰላለፍ ታዋቂ እና ሚዛናዊ ሲሆን ፣ ለማጥቃትም ይሁን ለመከላከል ተመራጭ ነው። አራት ተከላካዮች እና ሁለት አማካኝ ተከላካዮችን (ሲዲኤም) የሚጠቀም ሲሆን ከተቃራኒ ቡደን የሚመጡ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችል አይበገሬ ስልት ነው። በተጨማሪም ለቀሪዎቹ ፣ ሦስት አማካኝ አጥቂዎች እና አንድ ዋና አጥቂ ፣ የተለያዩ የጥቃት አማራጮችን ይሰጣሉ።
ጥቅም፡- ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት እና በርካታ የማጥቃት አማራጮችን ያሉት ሲሆን ፥ ጨዋታውን ለመቆጣጠር እና ልዩ የማጥቃት ዕድልን ይሰጣል።
4-4-2፡- ሁለገብ እና ሚዛናዊ የሆነው የ4-4-2 አሰላለፍ ፥ ማጥቃትም ይሁን መከላከል የሚያስችል ተመራጭ እና ታዋቂ አሰላለፍ ነው። ይህ አሰላለፍ ፥ መሃል አማካኞች የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾችን ቦታ ማስለቀቅ ፥ ሁለቱ አጥቂዎች የማያቋርጥ ጫና እንዲፈጥሩ እና የመሃል አማካኞች ኳስን በመቀማት ለአጥቂዎች ወደፊት ማከፋፈል ላይ ያተኩራል።
ጥቅም፡- የተመጣጠነ ፣ ተለዋዋጭ አሰላለፍ ሲሆን ፣ በተጨማሪም የመከላከል አቅምዎን ሳያዳክሙ ፣ ከፍተኛ የማጥቃት ጫናን ማሳደር ያስችልዎታል።
3-5-2፡- ይህ አሰላለፍ ፣ ጨዋታውን መቆጣጠር እና በርካታ የማጥቃት አማራጮችን የሚሰጥ ሲሆን ፥ ሶስት ተከላካዮችን የሚጠቀም ሲሆን ፥ አምስቱ መሃል አማካኞች (RM/LM) የማጥቃት እና የመከላከል ስራዎችን ሲሰሩ ፣ ቀሪዎቹ ሁለቱ አጥቂዎች እና የመሀል ሜዳ ኳስ አከፋፋይ ተጫዋቾች ደግሞ የጎል እድሎችን መፍጠር ላይ ይሰራሉ።
ጥቅም፡- ሰፊ የማጥቃት ዕድልን እና ፣ አማካኝ ክፍልን መቆጣጠር የሚያስችል አሰላለፍ ሲሆን ፣ ሆኖም ግን ጥሩ ጉልበት ያላቸው ተጫዋቾችን እና በአግባቡ የተደራጀ የተከላካዮች አሰላለፍን ይጠይቃል።
ከላይ ከተዘረዘሩት አሰላለፎች መካከል ፣ ከአጨዋወት ስልትዎ ፣ ምርጫዎ እና ከቡድንዎ ጋር የሚጣጣመውን በመምረጥ ፡ አጥጋቢ ውጤቶችን ለቡድንዎ ማስገኘት ይችላሉ።