
ከ20 ዓመታት በላይ ተከታታይ ሳምንታዊ ክፍሎቹን ለአድናቂዎቹን እያስተላለፈ ሲያስደስት የነበረው ዋን ፒስ አኒሜ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ረዘመ ያለ ዕረፍት ሊወስድ እንደሆነ ተነገረ ፥ ይሄም የሆነበት ምክንያት አዘጋጆቹ የዚህን ተወዳጅ አኒሜ የምስል ጥራቱ የማሳደግ እና የማሻሻል ዓላማ በመያዛቸው እና በጉጉት ለሚጠበቀው ኤግ-ሄድ አርክ ሙሉ ዝግጅታቸውን መጨረስ በመፈለጋቸው ፣ሚያዚያ 2025 በድጋሚ እንደሚመለስ በትዊተር ገፃቸው አሳውቀዋል።
ዘመኑን የሚመጥኑ የአኒሜሽን ቴክኖሎጂዎች ፣ የታሪኩ ጭብጥን ይበልጥ አጓጊ እና አስደሳች በማድረግ ህይወት እንደሚዘሩበትም ተናግረዋል። በተጨማሪም ዋን ፒስ ድጋሚ ሲመለስ አዲስ የስርጭት መርሃ-ግብር ይዞ የሚመለስ ሲሆን ፣ ጃምፕ ፊየስታ 2025 ላይ ተጨማሪ ዝርዝሮች የሚጋሩ ይሆናል። ምንም እንኳን ዋን ፒስ ለጊዜው መቋረጡ በአድናቂዎች ዘንድ ቅሬታን ሊፈጥር ቢችልም ፣ አዘጋጆቹ የምስል ጥራት ላይ ለመስራት እና አስደናቂ ተሞክሮን ለማቅረብ መወሰናቸው ያላቸውን ቁርጠኝነት እና ለተመልካቾቻቸው ያላቸውን ክብር በጉልህ ያሳያል።
እስከዚያው ድረስ ፣ አታክ ኦን ታይታንስን በሰራው ስቱዲዮ WIT አማካኝነት የዋን ፒስ ድጋሚ ስሪት የሆነው እና ሉፊ ከሰራተኞቹ ጋር ያደረገውን ቀደምት ጀብዱዎችን የሚያስቃኝ ዘመናዊ አኒሜሽን እየተዘጋጀ ሲሆን በመጪው አዲስ ዓመት ለተመልካቾች ለዕይታ የሚበቃ ይሆናል። ይህም የዋን ፒስ መውጫ ቀን እስኪደርስም ተመልካቾች በዚህ መዝናናት እንዲችሉ ዕድል ይሰጣል።
ምንም እንኳን የዋን ፒስ አድናቂዎች ኤግ-ሄድ አርክን ለመቀጠል እና የቬጋፐንክን ሚስጥራዊ መልዕክት ለማወቅ እስከ ሚያዚያ 2025 ድረስ መጠበቅ ቢኖርባቸውም ፥ መጭዎቹ ክፍሎች አስደሳች የምስል ጥራት ያላቸው አኒሜሽኖች በመሆናቸው ፣ ቅሬታውን ሊያስዎግድ ይችላል።