
በገንዚላ ጌምስ ተዘጋጅቶ የቀረበው ኦፍ ዘ ግሪድ በልዩ ፈጠራዎች የተሞላ እና በዘመነ ገጽታው ብዙዎችን ጉድ ያስባለ የሳይበርፐንክ FPS ጌም ነው። ይህን ጌም ብዙ ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች በዋናነት የሚጠቀሰው የብሎክቼን እና የNFT አማራጮችን ማካተቱ ሲሆን ፣ ይህም ብዙ ግርምትን እና ጥያቄዎችን አስነስቷል።
ኦፍ ዘ ግሪድ የNFT አማራጮችን በውስጡ ቢያካትትም ፣ ይህን አማራጭ የመጠቀም ወይም ያለመጠቀም ጉዳይ ሙሉ በሙሉ በተጫዋቾች ፍላቶት የሚወሰን ጉዳይ ነው። ተጫዋቾች NFTን መጠቀም ሳያስፈልጋቸው ጌሙን ሙሉ በሙሉ ማጣጣም ይችላሉ። እነዚህም በቁጥር ውስን የሆኑ NFTዎ በጌሙ ውስጥ በሚገኙ ፣ ሄክስ በተባሉ ልዩ ሳጥኖች ውስጥ ይገኛሉ።
እነዚህ የሄክስ ሳጥኖች ወደ NFT ሊቀየሩ የሚችሉ እና ገንዝ ብሎክቼን ላይ ሊሸጡ የሚችሉ የጦር መሳሪያዎችን ፣ አልባሳትን ፣ ማሻሻያዎችን በውስጣቸው ይዘዋል። ተጫዋቾች ይህ የመገበያያ መድረክ ላይ ፣ GUN Coinን በመጠቀም NFTታቸውን ፣ መግዛት እና መለወጥ ይችላሉ።
የኦፍ ዘ ግሪድ የብሎክቼይን ገጽታ ኖዶች ተብለው ከሚጠሩ ውስን ክፍሎች ጋር የተቆራኘ ነው። የሄክስ ሳጥን ውስጥ ያገኟቸውን ሽልማቶች ወደ NFTዎች ለመለወጥ ተጫዋቾች ከእነዚህ ኖዶች ውስጥ አንዱን መጐብኘት ይኖርባቸዋል ፣ እነዚህም ስጦታዎች የተረጋገጡ እና ልዩ የሆነ ዲጂታል ፊርማ የተደረገባቸው በመሆናቸው ለገበያ ሊቀርቡ ይችላሉ።
ይሁን እንጂ እነዚህ ኖዶች ውስን እና 10,000 ብቻ በመሆናቸው ለቀደምት ተጠቃሚዎች እና ገዥዎች ተሽጠዋል። ይህ ማለት አንድ ኖድ ላይ አንድ ግብይት በሚከናወንበት ወቅት የGUN Coin ኮሚሽን ወደ ኖዱ ባለቤት ይከፈላል።
የNFT አማራጩን የመጠቀም ፍላጐት የሌላቸው ተጫዋቾች ፣ ምንም ዓይነት መስተጋብር እንዲፈፅሙ የማይጠበቅባቸው ሲሆን ፣ ብሎክቼኑ ላይ ሳይሳተፉ ጌሙን ሙሉ በሙሉ ማጣጣም ይችላል። ሆኖም ግን ፍላጎቱ ላላቸው ፣ NFTዎችን መሸጥ ፣ መለወጥ ፣ እና የGUN Coin የማግኘት ዕድል ያገኛሉ።
ይህ አማራጭ አሁንም በማሻሻያ ሂደቶች ላይ መሆኑንን እና የGUN Coin በአሁኑ ጊዜ የሙከራ ኔትወርክ ላይ ብቻ እንደሚገኝ ልብ ማለት ይገባል።
ብሎክቼን እና NFTዎች በጌሞች ውስጥ ተወዳጅ እየሆኑ ሲሄዱ አንዳንድ ተጫዋቾች ሊፈጠሩ ስለሚችሉት አሉታዊ ተጽዕኖዎች እንደሚያሳስባቸው ገልፀዋል። ቢሆንም ኦፍ ዘ ግሪድ እነዚህን ባህሪያት እንደ አማራጭ እና ጌሙን በማይረብሽ መልኩ ለማቅረብ ያለመ ነው። ነገር ግን ፣ በብሎክቼን ላይ ምናባዊ ዕቃዎችን መግዛትና መገበያየት የሚያስከትለውን ጉዳትና ጥቅም መረዳት አስፈላጊ ነው።
እንደማጠቃለያ ፣ ኦፍ ዘ ግሪድ ተወዳዳሪ የጨዋታ ሜካኒክሶችን ከብሎክቼይን ጋር በማጣመር ልዩ አቀራረብን ያቀርባል። የNFTው ነገር አማራጭ ሆኖ ይቆያል ፣ ይህም ተጫዋቾች ይህን አማራጭን የመጠቀምም ይሁን ያለመጠቀም የመወሰን ነጻነት ሙሉ በሙሉ የእነሱ ሆኖ ይቆያል።