
በመጨረሻም አርኬን ምዕራፍ 2 ላይ ሲንጅድ ተብሎ የሚጠራው ገፀ-ባህሪ ድብቅ ማንነት ዶ/ር ኮሪን ሬቭክ መሆኑ ታውቋል። ዶ/ር ኮሪን ሬቭክ በአንድ ወቅት በፒልቶቨር አካዳሚ ውስጥ ታዋቂ አልኬሚስት የነበረ ሲሆን ፣ በተለያዩ እንስሳት ላይ ባደረጋቸው ሙከራዎች ይታወቃል ፥ ሆኖም ግን ዶ/ር ኮሪን ሬቭክ ግልጽ ባልሆኑ ምክንያቶች ከአካዳሚው እንዲሰናበት የተደረገ ሲሆን ፥ ይህን ጊዜ ነበር ህይወቱ ፍፁም ወደ ተለየ አቅጣጫ ያመራው። ይህንንም ተከትሎ ኦሪያናን የተባለች ሴት ልጁን ለማዳን በኬሚካል ፓምፖች የሚንቀሳቀስ የመስታወት ካፕሱል ውስጥ እንድትቆይ እስከማድረግ እና ሺመር እና ዋርዊክን የተባለ ጭራቅ እስከመፍጠር ድረስ የተለያዩ ሙከራዎችን በማድረግ ትልቅ መስዕዋትነትን ከፍሏል።
ኦሪያና League of Legends ላይ “The Clockwork Lady” በመባል የምትታወቅ ገፀ-ባህሪ ስትሆን ፥ አባቷ ኮሪን ሬቭክ በመርዛማ ጋዝ መመረዟን ተከትሎ ህይዎቷን ለማዳን ፥ የአካል ክፍሎቿን በማሽኖች እንደተካላት የህይዎት ታሪኳ ያትታል። አርኬን ይህን ታሪክ መሠረት በማድረግ እና ድጋሚ የሲንጅድ እና የኮሪን ሬቭክ ገፀ-ባህሪ በማዋሃድ ፣ ተስፋ የማይቆርጥ አባት አድርጎ አቅርቦታል። በዚህ ታሪክም ዶ/ር ሬቭክ/ሲንጅድ የኦሪያና ህይዎትን ለማዳን በሰው ሰራሽ መንገድ መኖር እንድትችል የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ያሳያል። የኦሪያና ፎቶ ያለበት የኪስ ሰዓቱም ፣ እሷን ደብቆ ያስቀመጠበትን ምስጢራዊ ክፍል መክፈቻ ቁልፍም እንደሆነ ታውቋል።
የዚህ ምስጢር መገለጥ ሲንጅድን ከአንድ እብድ ሳይንቲስትነት ወደ ጥልቅ ውስብስብ ገፀ-ባህሪነት ለውጦታል። ምንም እንኳን ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ ከሥነ-ምግባር አኳያ የሚያስወቅሱ ቢሆኑም ፣ ከጥልቅ የአባትነት ፍቅር እና ልጁን ለማዳን ካለው የማያወላውል ቁርጠኝነት እና በራሱ አገላለጽ ፣ “ያደረግሁትን ሁሉ ፣ ልጅን ለማዳን ነው" ብሎ ተገናግሯል። የቅርብ ጊዜ ሙከራው የሆነው ዋርዊክም ፣ የኦሪያናን ህይወት ማዳኛ ቁልፍ እንደሆነ እምነቱን ገልጿል። ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ልጁን ለማዳን የሚያደርጋቸው ከፍተኛ ጥረቶች ፣ የሲንጅድን ገፀ-ባህሪ ይበልጥ ውስብሰብ እና ሳቢ እንዲሆኑ አድርገውታል።
የዶ/ር ኮሪን ሬቭኬክ እውነተኛ ማንነት መገለጥ ገፀ-ባህሪውን ይበልጥ ጥልቅ እና ሳቢ በማድረግ የአርኬንን የታሪክ ጭብጥ ፍሰት ልብ አንጠልጣይ እና ስሜት ሰጪ አድርጎታል። በተጨማሪም ፣ አርኬን የLeague of Legends ታዋቂ ገፀ-ባህሪያትን በተለየ እና አስደሳች በመሆነ መልኩ የማቅረብ ብቃትን በተግባር አሳይቷል።