
ላይበርቲ ሲቲ ፕሪዘርቬሽን ሞድ፣ ያሸበረቀችውን እና ዘመናዊቷን ላይበርቲ ሲቲ ወደ GTA 5 ያመጣ፥ ከሁሉም በላይ ተጫዋቾች ከሎስ ሳንቶስ፣ ላይበርቲ ሲቲ ያለምንም እንከን መጓዝ እንዲችሉ ያስቻለ እና የGTA የረጅም ጊዜ አድናቂዎችን ህልም እውን ያደረገ ግሩም ፕሮጀክት ነበር።
ሆኖም ግን፣ እ.ኤ.አ ጃንዋሪ 16፣ 2025 ላይ አዘጋጆቹ በዲስኮርድ ገፃቸው ፕሮጀክቱ መሰረዙን በይፋ አሳውቀዋል። ፕሮጀክቱ "ከፍተኛ ትኩረት" መሳቡ እና ከሮክስታር ጌሞስ ጋር ስለጉዳዩ ያደረጉት ውይይት ለመሰረዙ ምክንያት እንደሆኑ ገልጸዋል።
ምንም እንኳን ምክንያቱ በግልጽ ባይገለጽም፣ ሁለቱም ሮክስታር ጌምስ እና ቴክ-ቱ ኢንተራክቲቭ ለመቋረጡ የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል የሚል ጭምጭምታ ቢኖርም፥ ሞዲንግ ቡድኑ በበኩሉ "ያለምንም ግጭት" እና ሁሉም ነገር "ሰላማዊ" በሆነ መንገድ ውሳኔ ላይ መደረሱን አስታውቋል።
ሆኖም ግን ስለጉዳዩ የተለያዩ መላምቶች እንደምክንያት ተቀምጠዋል፡-
የቅጂ መብት ጉዳዮች፦ ሞዱ የGTA 4 ንጥል-ክፍሎችን ይጠቀም የነበረ በመሆኑ፣ ይህ ደግሞ የሮክስታርን የቅጂ መብት ሊጥስ ይችላል።
የGTA 4 ድጋሚ-ስሪት፦ ሮክስታር በራሱ የGTA 4 ድጋሚ-ስሪትን እየሰራ ሊሆን ስለሚችል፣ ሞዱ የድርጅቱ ተቀናቃኝ እንዳይሆን በመፈለጉ።
ከፍተኛ ተቀባይነት፦ ፕሮጀክቱ ከፍተኛ ተቀባይነትን ማግኘቱ እና አላስፈላጊ ትኩረትን መሳቡ እንደምክንያት ሊጠቀሱ ይችላሉ።
ብዙ ተጫዋቾች ቅር የተሰኙ ሲሆን፣ የተደረገው ውሳኔ ፈጠራን የሚገድብ ነው ብለው ያምናሉ። አንዳንዶቹም በበኩላቸው ፋይሉ አስቀድሞ በሰፊው በመሰራጨቱ መዘጋቱ ተጫዋቾችን ከመጫወት ሊገድብ እንደማይችል እና ይህን ያህል ለውጥ እንደማይፈጥር ገልጸዋል።
ሮክስታር ጌምስ እና ቴክ-ቱ ኢንተራክቲቭ፣ ሞዶች ላይ እርምጃ ሲወስዱ ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው አይደለም። ይህም የGTA ሞዲንግ የወደፊት እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ጥያቄ ያስነሳል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሞዲንግ ቡድኑ የGTA ፕሮጀክቶች ላይ መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ እና በኣዲስ ፕሮጀክት እንደሚመለሱ ገልጸዋል።
በተጫዋቾች ዘንድ ቅሬታ ቢኖርም፣ አሁንም ወደ ላይበርቲ ሲቲ የመመለስ ፍላጎታቸው ጠንቅሮ እንደቀጠለ ነው። አንዳንድ ተጫዋቾች ሮክስታር GTA 4ን ድጋሚ ሰርቶ ያቀርበዋል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ። ለጊዜው ግን፣ ተጫዋቾች እ.ኤ.አ ማርች 4፣ 2025 የተለቀቀውን የGTA 5 እና የGTA ኦንላይን የፒሲ ማሻሻያ "Enhanced Edition" መኮምኮማቸውን ቢቀጥሉ ይመከራል።
የላይበርቲ ሲቲ ፕሪዘርቬሽን ሞድ ቢቋረጥም፣ ተጫዋቾች ለGTA ያላቸው ጥልቅ ፍቅር ግን ሁሌም ህያው ነው። አንገብጋዊው እና ዋናው ጥያቄ ግን፣ ሮክስታር የአድናቂዎችን ፍላጎት ራሱ ያሟላል ወይስ አዲስ የሞዲንግ ፕሮጀክቶች ማቅረቡን ይቀጥላል?
ወደፊት ምን እንደሚፈጠር አብረን እንጠብቃለን!