
ላለፉት ተከታታይ ወራት፣ ስለ ፎርትናይት እና የዋን ፒስ አጋርነት ብዙ ወሬዎች ሲናፈሱ ቆይተዋል፣ ሉፊ ፓይሬት ዎርልድ የኢፒክ ጌምስ ባትል ሮያል ላይ እየመጣ እንደሆነ በቅርቡ አፈትልከው የወጡ አዳዲስ መረጃዎች ጥቆማ ሰጥተዋል።
ይህ ሁሉ የተጀመረው እ.ኤ.አ በፌብሪዋሪ 2024 NotPaloleaks በለቀቃቸው መረጃዎች ሲሆን፣ ኢፒክ ጌምስ ባለ ሁለት ዙር አጋርነቶችን እያዘጋጀ መሆኑን ገልፇል።
1. ሁለት ዙር የገጸ-ባህሪያት አልባሳት (Skins) ይኖራሉ ተብሏል፡-
ዙር 1፦ እንደ ሉፊ፣ ናሚ፣ ዞሮ፣ ኡሶፕ እና ሳንጂ ያሉ ታዋቂ ገጸ-ባህሪያት ይካተታሉ።
ዙር 2፦ እንደ ብላክቢርድ፣ ዶፍላሚንጎ ወይም ሌሎች የስትሮው ሃት ቡድን አባላት ሊጨመሩ ይችላሉ።
2. ቀኑ በይፋ ባይገለጽም፣ ውስጥ አዋቂዎች እንዳሉት ከሆነ ይህ የአጋርነት ስምምነቱ የምዕራፍ 5 መገባደጃ ላይ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።
ኢፒክ ጌምስ ለሽርክናዎች እንግዳ አይደለም። ከናሩቶ፣ ድራጎን ቦል እና ምይ ሂሮ አካዳሚ በኋላ ዋን ፒስ ጌሙን መቀላቀሉ የማይቀር ይመስላል። የEiichiro Oda ስራ በዓለም ላይ ካሉት በጣም ታዋቂ የማንጋ ተከታታዮች አንዱ ሲሆን፣ በኔትፍሊክስ ላይ ያለው የቀጥታ ድርጊት ልምድም ተወዳጅነቱን ከፍ አድርጎታል።
ኢፒክ ጌምስ በትብብሮች ጊዜ አጓጊ የጨዋታ ልምዶችን ማቅረቡ የተለመደ ነው። አሁን ደግሞ የሚከተሉት ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡-
አዲስ አካባቢዎች፦ እንደልብዎ ሊያሰሷቸው የሚችሉ እንደ ታውዘንድ ሰኒ Thousand Sunny) ወይም ጎይንግ ሜሪ (Going Merry) ያሉ ቦታዎች።
ልዩ እቃዎች፦ የሉፊ ጎሙ ጎሙ ኖ ሚ (Gomu Gomu no Mi)፣ ተጫዋቾች እጆቻቸውን ለረጅም ርቀት ጥቃቶች እንዲዘረጉ የሚያስችላቸው እና ለአጭር ርቀት ውጊያ የሚሆኑ የዞሮ ታዋቂ ሰይፎች።
የጨዋታ ሁነታዎች፦ኢፒክ ጌምስ ከድራጎን ቦል ጋር ተመሳሳይነት ያለው፣ የዋን ፒስ ዩኒቨርስን መሠረት ያደረገ እና የባህር ላይ ጦርነቶችን ወይም የሀብት አደን የሚያካተት የተገደበ ጊዜ ሁነታን ሊያስተዋውቅ ይችላል።
እንደማንኛውም የአጋርነት ትብብሮች የተለያዩ አስተያየቶች ከተጫዋቾች የተሰነዘሩ ሲሆን፤ አንዳንድ ደስተኛ የሆኑ ተጫዋቾች፣ የሚወዷቸውን ገፀ-ባህሪያትን ፎርትናይት ላይ ለማየት የጓጉ ሲሆን፣ ጥርጣሬ ያደረባቸው ተጫዋቾች ደግሞ ከዋናው ማንጋ ጋር ወጥነት ላይኖረው ወይም ሊጋጭ ይችላል የሚል ስጋታቸውን ሰንዝረዋል።
እስካሁን ምንም ይፋዊ ማረጋገጫ ባይኖርም፣ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በተጫዋቾች መኃል የሚደረገው አዝናኝ ክርክር ተጧጡፎ መቀጠሉ፣ ይህን ሽርክና አስመልክቶ በተጫዋቾች ዘንድ ያለውን ከፍተኛ ጉጉት ያሳያል።