
Rockstar Games GTA 6ን አዘጋጅቶ ለመጨረስ ለማመን የሚከብድ በጀት ያወጣ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ከ1 ቢሊዮን እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ወጪ እንዳወጣ ታማኝ የመረጃ ምንጮች አመላክተዋል። ይህ እውነት ከሆነ፣ ከዚህ በፊት ከተሰሩ አንጋፋ ጌሞች ጋር ሲነፃጸር ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ወጪ የወጣበት ውዱ ጌም በመሆን ኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን ሪከርድ ይሰብራል። ነገሩን ግልጽ ለማድረግ ያህል፣ እ.ኤ.አ. በ2013 የተለቀቀው GTA V በወቅቱ 265 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ወጪ የወጣበት ሲሆን ይህም በራሱ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ቢሆንም፣ ከGTA6 ጋር ሲነጻጸር ግን እዚህ ግባ የሚባል አይመስልም።
ይህ ከፍተኛ መጠን ያለው በጀት ጌሙን ለማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን የሠራተኞች ደሞዝን፣ ቴክኖሎጂን፣ ጥበባዊ ፈጠራዎችን፣ ስክሪፕቶችን፣ የሙከራ ሂደቶዎችን፣ ዓለም አቀፍ የማስታወቂያ ዘመቻዎችንም ያካትታል። የትላልቅ ቪዲዮ ጌሞች በጀት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የሚሄድ ይመስላል። ሌላው የRockstar ተወዳጅ ጌም የሆነው Red Dead Redemption II ደግሞ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጥቶበታል።
ለምን ይህን ያህል በጀት አስፈለገ? የወጪውን መጋነን የሚያብራሩ በርካታ ምክንያቶች አሉ። በመጀመሪያ ደረጃ Rockstar ጌሙን እ.ኤ.አ ከ2014 ጀምሮ ማዘጋጀት የጀመረ ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ አዘጋጆች እና የፈጠራ ባለሙያዎችን በማሳተፍ ከአስር ዓመታት በላይ ዝግጅት አድርጎበታል። በተጨማሪም፣ የፈጠራ ወሰኑን ማስፋት የሚያስችሉ እጅግ የላቁ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀሙ ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ሰፊ፣ እና እውነታዊ ስሜት ያለው ዓለምን መፍጠር አስችሎታል። የማስታወቂያ ዘመቻዎቹ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጫዋቾችን ለመድረስ ያለመ ሲሆን መጠነ ስፋቱም ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ነው። በመጨረሻም፣ Rockstar ጥልቅ ታሪክን፣ ውስብስብ ገጸ-ባህሪያትን እና አሳታፊ የጨዋታ ልምድን ለመፍጠር ያለውን ግብዓቶች በሙሉ አሰባስቦ ጥቅም ላይ አውሏል።
ከፍተኛ ግምት የሆነውን 2 ቢሊዮን ዶላስ ብንወስድ፣ GTA 6ን ከመቼውም ጊዜ በላይ ውዱ ቪዲዮ ጌም የሚያደርገው ሲሆን፣ እንደ Star Citizen (ወደ 600 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ፣ አሁንም በዝግጅት ላይ የሚገኝ)፣ Destiny (500 ሚሊዮን ዶላር)፣ Cyberpunk 2077 (330 ሚሊዮን ዶላር) እና Call of Duty: Modern Warfare 2 (310 ሚሊዮን ዶላር) ያሉ ባለ ከፍተኛ በጀት ቪዲዮ ጌሞችን ሁሉ ቅርጥፍ አድርጎ ይበላቸዋል። ይህ ኢንቨስትመንት GTA 6ን ከትላልቅ የሆሊውድ ስራዎች ጋር ተነፃፃሪ፣ አልፎ ተርፎም በልጦ የሚገኝ ነው።
አንዳንድ ሰዎች የRockstar እና የአሳታሚው Take-Two Interactiveን ውሳቤ አደገኛ ቁማር በለው ቢፈርጁትም፣ ተንታኞች ግን ይህን ፍረጃ ስህተት እንደሆነ ገልፀዋል። የGTA ፍራንቻይዝ በቪዲዮ ጌም ታሪክ ውስጥ እጅግ በጣም ትርፋማ ከሆኑት ውስጥ አንዱ ሲሆን፣ GTA V በተለቀቀ በሶስት ቀናት ውስጥ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያገኘ ሲሆን GTA 6ም ከዚህ የበለጠ አስደናቂ ሽያጭን እንደሚያገኝ ተንታኞች አመላክተዋል። አንዳንድ ባለሙያዎች በበኩላቸው ጌሙ የወጣበትን በጀት አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መልሶ ማግኘት እንደሚችል ገልጸዋል።
እርስዎስ ምን ያስባሉ?