
ሰሞኑን ፎርትናይት ላይ ምስጢራዊ ጎንትሌቶች (Myst Gauntlets) ተለቀዋል። የዚህ ሲዝን ፊት አውራሪ መሆን ከፈለጉ እና ተቀናቃኞችዎን ማስጨነቅ ከፈለጉ፣ እነዚህን ጎንትሌቶች በአስቸኳይ እጅዎ ውስጥ ሊያስገቡ ይገባል። እንዴት ማግኘት እና ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚችሉ እንደሚከተለው አስቀምጠናል።
እነዚህን ጎንትሌቶች ማግኘት ቀላል፣ ሆኖም ግን ፈታኝ ሂደትን መወጣት ይጠይቃል። አብዛኛውን ጊዜ በጠላት አለቃዎች ተጥለው ወይም ካርታው ላይ በሚገኙ የተለያዩ ሚቲክ ሣጥኖች ውስጥ ይገኛሉ። ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የሚገኙበትን ቦታ አስቀድሞ ማወቅና ቦታው አቅራቢያ ቀድመው ቢገኙ ይመከራል። ሆኖም ግን እነዚህን ጋውንትሌቶች የሚያድኑ በርካታ ተጫዋቾች ስለሚኖሩ፣ ሊሰነዘርብዎ ለሚችል ማንኛውም ድንገተኛ ጥቃት ቀድመው ይዘጋጁ። ስለዚህ አካባቢውን በፍጥነት መቃኘታ እና ጥሩ የጦር መሳሪያና የፈውስ ግብዓቶች ማዘጋጀት ከቻሉ፣ የጠላት አለቃውን ወይም ሌሎች ተቀናቃኝ ተጫዋቾችን መጋፈጥ ይህን ያህል አዳጋች አይሆንብዎትም።
ኣስደሳቹ ክፍል የሚመጣው፣ እድል ቀንቶዎት አንዴ ጎንትሌቶቹ እጅዎ ውስጥ ካስገቡ በኋላ ነው። እነዚህ ጎንትሌቶች አስደናቂ ተከታታይና ፈጣን የመካከለኛ ርቀት ጥቃቶችን መሰንዘር የሚያስችሉዎት ሲሆን፣ ማንም ጫፋችንን አይነካንም ብለው መሽገው የተደበቁ ጠላቶችዎን ሳይቀር በቀላሉ ማጥቃት ይችላሉ። በዚህ ብቻ አያበቃም፣ ጎንትሌቶቹን በመጠቀም የህንፃ መዋቅሮችን በመደረማመስ፣ ወዲያውኑም ሻትጋናችሁን በመጠቀም ጠላቶችዎን መረፍረፍ ይችላሉ።
ሌላው፣ የእነዚህን ጎንትሌቶች የተንቀሳቃሽነት ብቃት መጠቀም ነው። ጎንትሌቶቹ ብዙውን ጊዜ ዳሽ (dash) ወይም ልዩ ዝላይ የማድረግ ብቃት ይሰጡዎታል። ይህንንም በፍጥነት ቦታ ለመቀየር፣ ከከባድ ተኩስ ለማምለጥ ወይም በጦርነት ወቅት ስልታዊ ቦታን ለመያዝ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። በተንቀሳቀሱ ቁጥር ጠላቶችዎ እርስዎን ማጥቃት እጅግ አዳጋች ይሆንባቸዋል።
ነገር ግን እንዲሁ ዝም ብለው ያለ ገደብ መጠቀም እችላለሁ ካሉ ተሳስተዋል። አስቸጋሪ እና ወሳኝ ሁኔታዎች ላይ ማምለጫ እንዳያጡ ሁልጊዜ እንደገና ጥቅም ላይ ለመዋል የሚወስድባቸውን ጊዜ በመከታተል ሊጠቀሙባቸው ይገባል። ስለዚህ ደኅንነትዎን ለአደጋ ሳያጋልጡ እና ጫና መፍጠርዎን ሳያቆሙ ለመቀጠል፤ የጦር መሳሪያዎችዎን እና ጎንትሌቶቹን በመቀያየር መጠቀም የሚመከር ስልታዊ አካሄድ ነው።