
ኒንቴንዶ፣ ስዊች 2ን ማጠናከሩን ቀጥሏል! አሁን ደግሞ ኮንሶሉ ፊቱን ወደ ስፖርት በማዞር ማሪዮ ቴኒስ ፊቨር የተሰኘ አዲስ ጌም ይዞ ሊቀርብ እንደሆነ አሳውቋል። ይህ ጌም የኒንቴንዶ ኮንሶል ላይ ብቻ የሚገኝ ሲሆን፣ ለፍሬንቻይዙ አስደናቂ ምዕራፍን ይዞ እንደሚመጣ ተነግሮለታል! እንዴት ካሉ? በአስደናቂ ሁኔታ፣ 38 ሊጫወቱባቸው የሚችሉ ገፀ-ባሕሪያትን የሚያካተት ሲሆን፣ ይህ እስካሁን በማሪዮ ቴኒስ ቪዲዮ ጌም ታሪክ ውስጥ እጅግ ትልቁ ነው።
ማሪዮ ቴኒስ፣ ኒንቴንዶ 64 ላይ ከተጀመረ ጀምሮ ለሁልም ተደራሽ፣ አዝናኝ እና አፎካካሪ ተሞክሮዎችን አንድ ላይ በማጣመር ለተጫዋቾች ሲያቀርብ ቆይቷል፤ አሁን ደግሞ ማሪዮ ቴኒስ ፊቨር የተሰኘው አዲስ ጌም ላይ ይበልጥ ልዩ የሆኑ ገፀ-ባሕሪያትን በማስተዋወቅ ነገሮችን ይበልጥ አስደሳች ለማድረግ በመዘጋጀት ላይ ነው። ማሪዮ፣ ሉዊጂ፣ ፒች፣ ዴዚ፣ ቦውሰር፣ ዮሺ እና ዶንኪ ኮንግ ሳይቀሩ እዚህ ጌም ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ በተጨማሪም ሮሳሊና፣ ፓውሊን፣ ካሜክ እና ቡም ቡምም ተካተዋል። በዚህ አያበቃም፣ የማሪዮ ጌሞች ላይ አልፎ አልፎ የምናያቸው ገፀ-ባሕሪያትንም ለመጀመሪያ ጊዜ በማካተት፣ ተጫዋቾች የተለያዩ ስልቶችን እንዲሞክሩ እና ልዩ ተሞክሮ እንዲያገኙ ዕድል ይሰጣል። ይበልጥ የሚያስደስተው ነገር ደግሞ፣ እያንዳንዱ ገፀ-ባሕሪያት የራሳቸው የሆነ ልዩ ችሎታ እና ስታይል ያላቸው በመሆኑ፣ ውድድሩን ይበልጥ ተለዋዋጭ እና አስደናቂ ያደርጉታል።
ኒንቴንዶ በማሪዮ ቴኒስ ፊቨር አማካኝነት የተጫዋቾቹን ቁጥር ከመጨመር ባለፈ፣ አስደናቂ የአጨዋወት ፈጠራዎችንም ጌሙ ላይ አክሏል። የውድድሮችን ሂደት ሙሉ በሙሉ ሊቀይር በሚችል ምልኩ፣ እያንዳንዱ ገፀ-ባሕሪያት የራሳቸው የሆነ ልዩ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው ተደርገው ነው የተዘጋጁት። እንዲሁም የቴኒስ ሜዳዎቹ ይበልጥ መስተጋብራዊ (interactive) እንዲሆኑ ተደርገው የተለያዩ ማሻሻያዎች ተደርጎባቸዋል! ይህም ሁኔታዎች ጋር በቀላሉ መላመድ እና ፈጣን መሆንን ከተጫዋቾች ይጠይቃል። በተጨማሪም፣ ሁለቱም ኦፍላይን እና ኦንላይን ሞዶች፣ በአንዴ እስከ አራት የሚደርሱ ተጫዋቾች አንድ ላይ እንዲጫወቱ ያስችሏቸዋል!
ኒንቴንዶ ለሁሉም የተጫዋች ዓይነቶች የሚመጥኑ በርካታ አዳዲስ ይዘቶችንም አዘጋጅቷል። ነጠላ እና ድርብ ግጥሚያዎች የተመለሱ ሲሆን፣ አዲስ Adventure Modeም ተጨምሯል! እንዲሁም ተጫዋቾች አነስተኛ RPG-style ታሪክ ውስጥ ከጠላት አለቆች ጋር በመፋለም የተለያዩ ተልዕኮዎችን የሚወጡ ይሆናል። ሌላው፣ የዓለም ሻምፒዮና የተባለ የሲዝን ደረጃዎች እና የመሪዎች ሠሌዳን ያካተተ ሞድ የሚገኝ ሲሆን፣ ተጫዋቾች በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ተጫዋቾች ጋር ኦንላይን እንዲወዳደሩ ያስችላቸዋል!
38 ገፀ-ባሕሪያትን፣ አዳዲስ መካኒኮችን፣ የተሻሻሉ አቀራረቦችን እና የስዊች 2ን ልዩ የፈጠራ አቅም ሙሉ በሙሉ በመጠቀም ማሪዮ ቴኒስ ፊቨር በ2026 ከሚለቀቁት ምርጥ ጌሞች መካከል ግንባር ቀደም ለመሆን በዝግጅት ላይ ይገኛል። ኒንቴንዶ የጌም ስብስቦቹን ማስፋፋቱን ቀጥሏል! ይህም ኮንሶሉ፣ መዝናናትን ለሚሹ ቤተሰቦች እና ቀንደኛ ተፎካካሪ ተጫዋቾችን የሚመጥኑ ጌሞችን ማቅረብ ቀዳሚ ዓላማው መሆኑን ትልቅ ማሳያ ነው።