
እ.ኤ.አ በ2023 የመጀመሪያው ሱፐር ማሪዮ ብሮስ ፊልም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ስኬትን ያገኘ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ኒንቴንዶ እና ኢሉሚኔሽን ስቱዲዮ በከፍተኛ ጉጉት የሚጠበቀውን ሱፐር ማሪዮ ጋላክሲ ፊልም ሊለቀቅ እንደሆነ በይፋ አሳውቀዋል። እ.ኤ.አ ኤፕሪል 2026 ላይ ሊለቀቅ ቀጠሮ የተያዘለት ይህ ፊልም ተወዳጆቹን ሱፐር ማሪዮ ጋላክሲ እና ሱፐር ማሪዮ ጋላክሲ 2 ጌሞች መነሻ በማድረግ የተሰራ ሲሆን፣ የማሪዮንና የጓደኞቹን የከዋክብት ጉዞ ለተመልካቾ የሚያስቃኝ ይሆናል።
የመጀመሪያው በቀለማት ያሸበረቀ ዩኒቨርስና የፍራንቻይሱን ይዘት በጠበቀ መልኩ የቀረበው ፊልም ተመልካቾችን ማስደመም ችሎ ነበር። በሁለተኛው ክፍል ኒንቴንዶ እና ኢሉሚኔሽን የታሪኩን መቼት ወደ ጠፈር በመውሰድ፥- ማሪዮ፣ ሉዊጂ፣ ፒች እና ቦውዘር፣ የጋላክሲው መሪ ገፀ-ባሕሪያት ከሆኑት ሉማስ ጋር በመሆን በምስጢራዊቷ ሮሳሊና እየተመሩ ወደ ተለያዩ አዳዲስ ፕላኔቶች እና ጋላክሲዎች ጉዞዎችን ያደርጋሉ።
ይህ ፊልም አሁንም ድንቅ ተዋንያኖች የሚሳተፉበት ሲሆን፦ ክሪስ ፕራት እንደ ማሪዮ፣ ቻርሊ ዴይ እንደ ሉዊጂ፣ አንያ ቴይለር-ጆይ እንደ ፒች፣ እና ጃክ ብላክ በድጋሚ ቦውሰርን በመሆን ይጫወታሉ። እንዲሁም ሴት ሮገን፣ ኪጋን-ሚካኤል ኪ እና ፍሬድ አርሚሰን የቀድሞ ሚናቸውን ድጋሚ የሚጫወቱ ሲሆን፣ አሮን ሆርቫት እና ሚካኤል ጄሌኒክ በዳይሬክተርነት፣ ማቲው ፎጌል ደግሞ ስክሪፕት ጸሃፊነት ይመለሳሉ። ማጀቢያ ሙዚቃዎቹ የመጀመሪያውን ፊልም ማጀቢያ ባዘጋጀው ብራያን ታይለር የሚቀናበሩ በመሆናቸው መሳጭ ሙዚቃዎችን ይጠብቁ።
ፊልሙ ኤፕሪል 1 በአሜሪካ እና ኤፕሪል 24 በጃፓን ለእይታ ከመቅረቡ በፊት በፈረንሳይ እ.ኤ.አ. ኤፕሪል 1፣ 2026 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ለተመልካቾች ለእይታ ይበቃል። ይፋዊ ማስታወቂያው የተደረገው የሱፐር ማሪዮ ብሮስ 40ኛ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀ ልዩ የኒንቴንዶ ዳይሬክት ላይ መሆኑም የፕሮጀክቱ ትልቅነት ጎልቶ እንዲታይ አድርጓል።
በዚህ ሁለተኛ ክፍል ኒንቴንዶ ማሪዮን ወደ ሲኒማዊ ገፀ-ባሕሪ ለመቀየር ያለው ፍላጎት በእጥፍ የጨመረ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ፊልም በቦክስ ኦፊስ ከ1.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ በአዲሱ ክፍል ደግሞ ይበልጥ አስደናቂ ትዕይንቶችን፣ አዳዲስ ፕላኔቶችን እና ትልቅ የፊልም ዝግጅት ቡድን በማዋቀር የመጀመሪያው ክፍል ካስገኘው ስኬት በላይ ለማስመዝገብ ታልሟል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኒንቴንዶ እ.ኤ.አ በ2027 ለመልቀቅ ያቀደውን ዘ ሌጀንድ ኦፍ ዜልዳ ፊልም እና ሌሎች ፕሮጀክቶች ማዘጋጀቱን እና በሲኒማ ዘርፉ ላይ ያለውን ተሳትፎ ማስፋፋቱን የቀጠለ ሲሆን፣ ይህም የኒንቴዶ የፊልም ጉዞ ገና መጀመሩን ማሳያ ነው።