
Counter-Strike 2 (CS2) ዝም ብሎ ረጅም ሰዓት በመጫወት ብቻ የኢላማ ብቃትን ማሳደግ አይቻልም። ነገር
ግን፣ በደንብ የተዋቀረ የ15 ደቂቃ ልምምድ ማድረግ፣ ወደ ጨዋታው ስትገቡ በራስ መተማመናችሁ ጨምሮ፣
ኢላማችሁ ዝንፍ የማይል ሆኖ እና ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ሆናችሁ እንድትገኙ ይረዳችኋል። ደስ የሚለው ነገር፣ ይህ
ዘዴ ጊዜ በሌላችሁ ወቅት እንኳ በቀላሉ ልትተገብሩት የምትችሉት ነው።
ለመጀመሪያዎቹ 5 ደቂቃዎች ዋናው ግባችሁ ነጥብ መሰብሰብ ሳይሆን እጃችሁን ለጨዋታው ማዘጋጀት እና
ማፍታታት ነው። የHS-only deathmatch ወይም ክላሲክ aim map ላይ በመግባት ያለመቻኮል መጫወት
ጀምሩ። በመቀጠል የመሳሪያችሁ አነጣጣሪ (crosshair) ሁልጊዜም የጠላት ጭንቅላት ጋር እኩል መሆኑን (head
level) እና እዛው ላይ እጃችሁን መርጋቱን አረጋግጡ። ያለ አግባብ ዝም ብላችሁ ጥይት ማርከፍከፍ ወይም
እጃችሁን ማወዛውዝ የለባችሁም፤ ይልቁንም ዒላማውን የጠበቀ እና የተረጋጋ ተኩስ ለማድረግ ጥረት አድርጉ።
ለቀጣዮቹን 4 ደቂቃዎች ደግሞ፣ ተንቀሳቃሽ ኢላማዎች የሚገኙበት ማፕ ላይ በመግባት የተንቀሳቃሽ ኢላማ
ጭንቅላት ላይ ለጥቂት ሰከንድ ሳትተኩሱ በማነጣጠር፣ ወዲያው ቃታውን በመሳብ ጭንቅላቱን አፈንዱት። ይህ
ልምምድ በድንገት ከመደናገጥ ይልቅ ትናንሽ እና ትክክለኛ ማስተካከያዎችን እንድታደርጉ ያስተምራችኋል። ይህም
በተለይ በመካከለኛ ርቀት ላይ ለሚደረጉ ውጊያዎች እጅግ ወሳኝ ነው።
ከዛም ለቀጣይ 3 ደቂቃዎች ማነጣጣሪያችሁን በሁለት ኢላማዎች መኃል አድርጉ፤ እና በፍጥነት ወደ አንዱ ኢላማ
ራስ በመመለስ አንድ ጥይት ብቻ ተኩሱና ወደ መነሻችሁ ኢላማ ነጥብ ተመለሱ። ፍጥነት ላይ አታተኩሩ፤
ይልቁንም ያልተዛነፈ የኢላማ ነጥብ መያዝ ላይ አተኩሩ፤ የኢላማ ክህሎታችሁ ሲዳብር ፍጥነታችሁም አብሮ
እያደገ ይመጣል።
የመጨረሻዎቹን 3 ደቂቃዎች በመደበኛ deathmatch ላይ በማሳለፍ ልክ እንደ እውነተኛ ጨዋታ
እየተንቀሳቀሳችሁ ተኩሱ። ወደ ጎን ተንቀሳቀሱ፣ ቁሙ፣ ተኩሱ፣ ከዚያም ቦታችሁን ቀይሩ። እስካሁን
የተለማመዳችሁትን ሁሉ ያለምንም ጭንቀት ደጋግማችሁ ተግብሩት። ይህም ደረጃ አዕምሯችሁ ልምምዱን
ከእውነተኛው ጨዋታ ጋር የሚያቆራኝበት ነው።
ይህ የልምምድ ዘዴ አጭር፣ ተደጋጋሚ እና ግልጽ ግብ ያለው በመሆኑ ውጤታማ ያደርጋችኋል። እነዚህን
ልምምዶች ጨዋታ ከመጀመራችሁ በፊት ካከናወናችሁ፣ ገና ጨዋታውን እንደጀመራችሁ የምትስቱት የጥይት
ቁጥር እየቀነሰ፣ በራስ መተማመናችሁ ደግሞ ሲጨምር ታያላችሁ።
መልካም ልምምድ