
GTA RP በGrand Theft Auto Vን መሠረት በማድረግ መሳጪ ተሞክሮን ከሚያቀርቡ ጌሞች መካከል ግንባር
ቀደሙ ነው። GTA RP ላይ ተራ መደበኛ ተጫዋች መሆናችሁ ይቀርና የራሳችሁ የኋላ ታሪክ፣ ማንነት እና
ለምትወስኑት እያንዳንዱ ውሳኔ የአፀፋ ምላሽ እና ተጠያቂ የሚሆን ገፀ-ባሕርይ ይኖራችኋል። ወደዚህ ዓለም
ከመቀላቀላችሁ በፊት፣ ዓለም አቀፍ ዝናን ያተረፉ ሰርቨሮችን እና ከምንም በላይ ደግሞ ጨዋታው የሚመራባቸው
ደንቦችን ማወቅ ግድ ይላችኋል፤ ይህ ካልሆነ ግን ውጥናችሁ ገና ከጅምሩ ሊቀጭ ይችላል።
ዓለም አቀፍ ዝናን ካተረፉ አንጋፋ ሰርቨሮች መካከል NoPixel ዋነኛው ነው። አስደናቂ የታሪክ ፍሰት አቀራረብን
ጥብቅ ሚናን መሠረት ያደረገ የአጨዋወት (RP standard) ሂደትን ያጣመረ በመሆኑ፣ በተለይ በታዋቂ
ስትሪመሮች ዘንድ እጅግ ታዋቂነትን ያተረፈ ነው። ወደዚህ ሰርቨር መግባት አስቸጋሪ እና ጥብቅ የምልመላ ሂደትን
የሚከተል ቢሆንም፣ ምርጥ እና አስደሳች ተሞክሮን ለሚሹ ተጫዋቾች ተቀዳሚ አማራጭ ነው።
ይበልጥ ተደራሽ የሆነው GTA World ደግሞ በጽሑፍ ላይ የተመሠረተ የሚና አጨዋወትን (text-based RP)
የሚከተል ሲሆን፣ ወጥ የሆነ እና ቁምነገር አዘል አጨዋወትን የምትፈልጉ ከሆነ ጥሩ አማራጭ ነው። Eclipse RP
ደግሞ ኢኮኖሚ፣ ሥራዎች እና ዘላቂነት ያላቸው መስተጋብሮች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሌላ አሪፍ አማራጭ
ነው። በተጨማሪም PurpleRP ወይም LegacyRP ለጀማሪ ተጫዋቾች ምቹ እና የሚና አጨዋወት
ይዘታቸውን ሳይለቁ ቀለል ያለ አቀራረብ ያላቸው በመሆኑ ጥሩ አማራጮች ናቸው።
ዋናው ማወቅ ያለባችሁ ጉዳይ የትኛውንም ሰርቨር ብትመርጡ ደንቦችን ማወቅ እና ለሕጎች ተገዢ መሆን ምንም
የማያወላውል ጥብቅ ጉዳይ መሆኑን ነው። ዋነኛው እና የመጀመሪያው ሕግ Zero Metagaming ነው። ይህም
ማለት፣ ገፀ-ባሕርያችሁ የሚያውቀው በጨዋታው ውስጥ ያየውን፣ የሰማውን ወይም ያጋጠመውን ብቻ ነው።
ስለዚህ ከጨዋታው ውጭ ወይም በገሃዱ ዓለም ያገኛችኋቸውን መረጃዎች እና ስትሪሞችን ወይም ዲሰኮርድን
በመጠቀም ጨዋታው ውስጥ ለመተግበር መወሰን ወዲያውኑ ከሰርቨሩ ሊያስባርራችሁ ይችላል።
ሌላው ወሳኝ ጉዳይ ደግሞ ለሕይወት ዋጋ መስጠት ነው። ገጸ-ባሕርያችሁ ለሕይወቱ የሚሳሳ እና የሚጨነቅ
በመሆኑ፤ ያለምንም በቂ ምክንያት ራስን ለአደጋ ማጋለጥ ወይም ለሞት የሚያደርሱ ድርጊቶችን መፈጸም
በፍጹም የተከለከለ ነው።
በተጨማሪም ከፓወርጌሚንግ ማለትም ሌሎች ተጫዋቾች ሚናቸውን እንዳይጫወቱ እንቅፋት መሆን ወይም
ተጨባጭነት የሌላቸውን ድርጊቶች ከመፈጸም መታቀብ ይኖርባችኋል። GTA RP በጋራ የምታጣጥሙት ተሞክሮ
እንጂ እኔ እብስ፣ አንተ ትብስ የምትባባሉበት ውድድር አይደለም፤ ግቡ ማሸነፍ ወይም መሸነፍ ሳይሆን ሊያኮራ
የሚችል ታሪክ በጋራ መገንባት ነው።
በመጨረሻም፣ ጊዜ ወስዳችሁ ግልጽ እና ተጨባጭነት ያለው ገጸ-ባሕርይ ለመፍጠር ሞክሩ። ገጸ-ባሕሪያችሁ
ይበልጥ ተፈጥሯዊ በሆነ ቁጥር፣ የጨዋታ ተሞክሯችሁም በዛኑ ልክ ጣፋጭ እና የማይረሳ ይሆናል። GTA RP
ትዕግሥትን፣ መደማመጥን እና ደንቦችን ማክበርን የሚሻ ጨዋታ ነው።
መልካም ጨዋታ